Numbers 11

ከእግዚአብሔር የወረደ እሳት

1በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ስለ ደረሰባቸው ችግር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ አጕረመረሙ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ማጕረምረማቸውን በሰማ ጊዜ በጣም ተቈጣ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) እሳት በመካከላቸው ነደደች፤ ከሰፈሩም ዳርቻ ጥቂቱን በላች። 2ሕዝቡ ወደ ሙሴ ጮኸ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ፤ እሳቲቱም ጠፋች። 3ከዚህ የተነሣም የቦታው ስም፣ “ተቤራ”
ተቤራ ማለት ማቃጠል ማለት ነው።
ተባለ፤ የእግዚአብሔር (ያህዌ) እሳት በመካከላቸው ነዳለችና።

እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የላከላቸው ድርጭት

4ድብልቁ ሕዝብ ሌላ ምግብ ጐመጀ፤ እስራኤላውያንም እንዲህ እያሉ ያጕረመርሙ ጀመር፤ “ምነው የምንበላው ሥጋ ባገኘን ኖሮ! 5በግብፅ ያለ ምንም ዋጋ የበላነው ዓሣ እንዲሁም ዱባው፣ በጢኹ፣ ኵራቱ፣ ነጭ ሽንኵርቱ ትዝ ይለናል። 6አሁን ግን የምግብ ፍላጎታችን ጠፍቷል፤ ከዚህ መና በስተቀር የምናየው የለም!”

7መናው እንደ ድንብላል ዘር ትንንሽ ሆኖ የሙጫ መልክ ነበረው። 8ሕዝቡ ተዘዋውሮ በመልቀም በወፍጮ ከፈጨ ወይም በሙቀጫ ከወቀጠ በኋላ በምንቸት ይቀቅለው ወይም ይጋግረው ነበር፤ ጣዕሙም በወይራ ዘይት የተጋገረ ያህል ይጣፍጥ ነበር። 9ጤዛው ሌሊት በሰፈር ላይ በሚወርድበት ጊዜ መናውም እንዲሁ ይወርድ ነበር።

10ሙሴ፣ ሕዝቡ ሁሉ በየቤተ ሰቡ፣ በየድንኳኑ ደጃፍ ሆኖ ሲያለቅስ ሰማ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እጅግ ተቈጣ፤ ሙሴም ተጨነቀ። 11እርሱም እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “እንዲህ ያለውን መከራ በባሪያህ ላይ ለምን አመጣህ? የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም የጫንህብኝስ ምን አስቀይሜህ ነው? 12ይህን ሁሉ ሕዝብ የፀነስሁት እኔ ነኝን? እኔስ ወለድሁትን? ታዲያ ሞግዚት ሕፃን እንደምትታቀፍ በክንዴ ታቅፌ ለቀድሞ አባቶቻቸው ትሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባህላቸው ምድር እንዳስገባቸው የምትነግረኝ ለምንድን ነው? 13ለዚህ ሁሉ ሕዝብስ ሥጋ ከወዴት አመጣለሁ? ሁሉም ‘የምንበላው ሥጋ ስጠን’ እያሉ ያለቅሱብኛል። 14እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም። 15እንዲህስ ከምታደርገኝ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ አሁኑኑ ግደለኝ፤ የሚደርስብኝን ጥፋት አልይ።”

16 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ መካከል በመሪነትና በእልቅና ብቃት አላቸው የምትላቸውን ሰባ የእስራኤል ሽማግሌዎች አምጣልኝ፤ ካንተም ጋር ይቆሙ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዲመጡ አድርግ። 17ወደዚያም ወርጄ አነጋግርሃለሁ፤ ባንተ ላይ ካለው መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቡንም ሸክም ብቻህን እንዳትሸከም እነርሱ ያግዙሃል።

18“ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ነገ ሥጋ ትበላላችሁና ራሳችሁን በመቀደስ ተዘጋጁ። “በግብፅ ተመችቶን ነበር፤ አሁን ግን ሥጋ ማን ይሰጠናል!” ብላችሁ ያለቀሳችሁትን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰምቷል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ትበላላችሁ። 19የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ወይም ለአምስት፣ ለዐሥር ወይም ለሃያ ቀን አይደለም፤ 20ነገር ግን በአፍንጫችሁ እስኪወጣና እስኪያንገፈግፋችሁ ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ፤ በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ንቃችሁ በፊቱ፣ “ለምን ከግብፅ ወጣን?” ብላችሁ አልቅሳችኋልና።’ ”

21ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እነሆ እኔ በስድስት መቶ ሺሕ እግረኛ መካከል እገኛለሁ፤ አንተ ደግሞ ‘ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ’ ብለሃል፤ 22ታዲያ ስንት የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋ ቢታረድላቸው ይበቃ ይሆን? በባሕር ያለው ዓሣ ሁሉ ቢያዝ ሊዳረሳቸው ይችላልን?”

23 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለሙሴ፣ “በውኑ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክንድ ይህን ያህል ዐጭር ነውን? የነገርሁህ ቃል እውነት መሆን አለመሆኑን አሁኑኑ ታየዋለህ” ሲል መለሰለት።

24ሙሴም ወጣና እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎች ሰባውን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረጋቸው። 25ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወርዶ ተናገረው፤ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈሱ ባደረባቸውም ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደገሙትም።
ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላም ትንቢት መናገራቸውን አላቆሙም የሚሉ አሉ።


26ኤልዳድና ሞዳድ የተባሉ ሁለት ሰዎች ግን ሰፈር ውስጥ ቀርተው ነበር፤ እነርሱም ከሽማግሌዎቹ ጋር ተቈጥረው ሳለ ወደ ድንኳኑ አልሄዱም ነበር፤ ሆኖም የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱም ላይ ስላደረባቸው ሰፈር ውስጥ እያሉ ትንቢት ተናገሩ። 27አንድ ወጣትም ሮጦ በመሄድ፣ “ኤልዳድና ሞዳድ ሰፈር ውስጥ ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው።

28ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱም ተነሥቶ፣ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፤ ከልክላቸው እንጂ” ሲል ተናገረ።

29ሙሴ ግን መልሶ፣ “ስለ እኔ ተቈርቍረህ ነውን? የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፣ እግዚአብሔርም (ያህዌ) መንፈሱን ቢያሳድርባቸው ምንኛ ደስ ባለኝ!” አለ፤ 30ከዚያም ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ሰፈር ተመለሱ።

31በዚህ ጊዜ ነፋስ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወጥቶ ድርጭቶችን ከባሕር ወደ ሰፈር አመጣ፤ በየአቅጣጫውም ከፍታው ሁለት ክንድ፣
አንድ ሜትር ያህል ነው።
ርቀቱም የአንድ ቀን መንገድ ያህል እስኪሆን ድረስ በሰፈሩ ዙሪያ ከመራቸው።
32በዚያን ዕለት ቀንና ሌሊቱን በሙሉ፣ በማግሥቱም ሙሉውን ቀን እንደዚሁ ሕዝቡ ወጥቶ ድርጭቶች ሰበሰበ፤ ከዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ ያነሰ የሰበሰበ ማንም አልነበረም፤ የሰበሰቡትንም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ አሰጡት። 33ነገር ግን ሥጋው ገና በጥርስና በጥርሳቸው መካከል ሳለ አላምጠው ሳይውጡት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በላያቸው ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት ክፉኛ መታ። 34ሌላ ምግብ ለማግኘት የጐመጁትን ሰዎች በዚያ ስለ ቀበሯቸው የቦታው ስም “ቂብሮት ሃታአባ”
የምኞት መቃብር ማለት ነው።
ተባለ።

35ሕዝቡም ከቂብሮት ሃታአባ ወደ ሐጼሮት ተጕዘው እዚያው ሰፈሩ።

Copyright information for AmhNASV